የሰንበት ገበያ ማዕከላት ህብረተሰቡ የተለያዩ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ያስችላል:- ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር) ታህሳስ 09፣2018 ዓ/ም ቡታጅራ የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት በከተማዉ ሁለተኛውን "ከሰንበት እስከ ሰንበት" የገበያ ማዕከል በዛሬው እለት በይፋ አስጀምሯል። የገበያውን ማዕከል በሥፍራው ተገኝተው የጎበኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ባዩሽ ተስፋዬ እንደገለፁት የሰንበት ገበያ ማዕከላት ህብረተሰቡ የተለያዩ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱ ያግዛል ብለዋል። መንግስት ቦታ እና ግብር ለአቅራቢዎቹ ከየትኛውም ክፍያ ነፃ በማድረግ ለህብረተሰቡ እንዲጠቅሙ እያገዛ ስለመሆኑ ያነሱት ዶ/ር ባዩሽ አምራቹን ከሸማቹ ጋር የማስተሳሰር ሥራም እየተሰራ ስለመሆኑ አመላክተዋል። በሰንበት ገበያ ማዕከላት በዋናነት ጥራት ያለዉ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገኝ ይፈለጋል ያሉት የቢሮዉ ኃላፊዋ ለዚህም ድጋፍ በሚያስፈልገው ሁሉ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዉ በየጊዜው ክትትል እና ቁጥጥር ያስፈልጋል ነዉ ያሉት። ተደራሺነቱን የማስፋፋት ሥራዎችን በመሥራት የአገልግሎት ማዕከላቱን ማበራከት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል። የከምባታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሞላልኝ አብርሃም የሰንበት ገበያ ዋናዉ አላማ ሸማቹ ህብረተሰብ ክፍል ጥራት ያለዉን ምርት ማግኘት የሚችልበት ምቹ እድል መፍጠር ስለመሆኑ ገልፀዉ አቅራቢዎችም ይህንን በአግባቡ በመገንዘብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግና ኢኮኖሚዉን ለማረጋጋት የተጀመረ ኢንሼቲቭ ስለመሆኑ ገልፀዋል። መንግስት ከግብር እና ከቤት ክራይ ነፃ ያደረገበት ምክንያት የዋጋ ልዩነት በመፍጠር ሸማቹን ብሎም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ አመላክተዋል። የምርት አቅርቦትን ትስስር ከአምራቹ ጋር በመፍጠር ተግባሩ ያለማቋረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል በማለት ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ለሰጠዉ ልዩ ትኩረት አመስግነዋል። የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ በበኩላቸው በሂደቱ የሚፈጠሩ ዉስንነቶች በመቅረፍ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተማ አስተዳደሩ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል። በቀጣይ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን በበቂ መልኩ በማምጣት አፅንኦት ሰጥተዉ እንደሚሰሩ ጭምር አስገንዝበዋል። በመርሐ-ግብሩም የከምባታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ተስፋዬን ጨምሮ የክልል ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።