Skip to main content
tmdnews2

የአንጋጫ ዘመናዊ የሰብል ግብይት ማዕከል ግንባታ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ ከተቋራጭ የግንባታ ድርጅት ጋር የዉል ስምምነት መደረገጉ ተገለተጸ። የካቲት 28/2017 ዓ/ም ቡታጅራ በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ከምባታ ዞን በአንጋጫ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው አንጋጫ ዘመናዊ የሰብል ግብይት ማዕከል ግንባታ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ ከግንባታ ተቋራጭ ድርጅት ጋራ የዉል ስምምነት ተደረጓል። የማዕከሉ ቀሪ ግንባታ በ60 ቀናት ዉስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል። የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገበያ ልማትና ግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ዋጄቦ በስምምነቱ ወቅት እንገለፁት የአንጋጫ ዘመናዊ የሰብል ግብይት ማዕከል ግንባት ስራ በቀድሞ ደቡብ ክልል የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑን አስታዉሰዉ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታዉ ሂደቱ በመጓተቱ በአከባቢዉ ማህበረሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ እንዲጠናቀቁ ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት የአንጋጫ ዘመናዊ የሰብል ግብይት ማዕከል የግንባታ ሂደት ባጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በዛሬዉ ዕለት ከግንባታ ተቋራጭ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል። አሁን ላይ የግንባታ ስራዉ 85 በመቶ መጠናቀቁን የገለፁት ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ ቀሪ የግንባታዉ ስራ ሲጠናቀቅ አርሶ አደሩን በዘመናዊ የግብይት ስርዓት ከማሳተፍ በተጨማሪ ሸማቹን ከአምራቹ በቀጥታ በማገናኘት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል። ማዕከሉ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ለአምራቹ የገበያ ትስስር በመፍጠር ለህብረተሰቡ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ከወረዳዉ አስተዳደር ጀምሮ የአከባበከዉ ማህበረሰብ ማዕከሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የአንጋጫ የሰብል ገብይት ማዕከል በከተማዉ ከተጀመሩ የልማት ስራዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት የአንጋጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘሪሁን ተክሌ ተቋርጦ የነበረዉን የግንባታ ስራ እንዲጀመር ከፍተኛ ጥረት ላደረገዉ ለክልሉ ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል። አከባቢዉ በከፍተኛ ሁኔታ የሰብል ምርት የሚመረትበት በመሆኑ ግንባታዉ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ሸማቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። የአዲስ ራዕይ የግንባታ ተቋራጭ ተወካይ አቶ ደሳለኝ ኢሬሻ በዉል ስምምነቱ ወቅት እንደገለፁት ግንባታዉ ከተያዘለት ግዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ከወዲሁ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ መጀመሩን ገልፀዉ በተገባዉ ዉል መሰረት ሁሉም ባለድርሻ አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የማዕከሉን የግንባታ ስራ አዲስ ራዕይ የግንባታ ተቋራጭ የሚያከናዉን ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ወጪውን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እንደሚሸፍን ተገልጿል። የገበያ ማዕከሉ በውስጡ የእህል መጋዘንና ብዙ ቁጥር ያላቸው የመሸጫ ክፍሎች ያካተተ ነዉ። በዉል ስምምነቱ የክልሉ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ተወካይ፣ ከክልል: ከዞን/ ከከተማ አስተዳደርሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ/ፅ/ቤት የተገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።